በ2ዐ18 በጀት ዓመት የተሰጠውን ስልጠናና ምዘና በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት በአዳማ ከተማ ሪፖርት ቀረበ
የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት በከተማ ፕላን፣ መሬት እና በከተማ ፋይናንስ ዘርፍ ስራዎች የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት እና በሙያቸው ብቁ በማድረግ ለነዋሪዎቻቸው የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በ2018 በጀት ዓመት ለ8ኛ ዙር በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች (አምቦ፣ አዳማ፣ ባህርዳር፣ ድሬዳዋ እና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች) የሰጠውን የስልጠናና ምዘና የመዝጊያ መርሃ-ግብር አካሄደ፡፡
መድረኩን የከፈቱት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አበበ ፈለቀ እንደተናገሩት ስልጠናውና ምዘናው የከተማ አስተዳደር ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ፤ የማዘጋጃ ቤት አካላትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ እና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ዕውን በማድረግ የህዝብን እርካታ ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የሰው ኃይል ልማት ስራዎችም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በንግግራቸው ማጠቃለያም የስራ ኃላፊዎች የሙያ ስልጠና ወስደው ምዘናውን ያለፉ ባለሙያዎችን በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍና በሚመጥናቸው ቦታ በመመደብ ዕውቀታቸውን ለህዝብ አገልግሎት እንዲያውሉ ጠንካራ የአሠራር ስርዓት በመዘርጋት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ በ2018 በጀት ዓመት የተካሄደውን ስልጠናና ምዘና በማስመልከት የተዘጋጀውን ሪፖርት አቶ መቅሱድ ኸይሩ፣ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የአቅም ግንባታና ኮሙዩኒኬሽን አሀድ አስተባባሪ አቅርበዋል። ከደረጃ ሁለት እስከ ደረጃ አምስት ባሉ የሙያ ደረጃዎች በአምስት ቁልፍ ስትሪሞች ማለትም (Cadastral Surveying, Cadastral Registry, Urban Planning, Real Property Valuation እና Urban Finance)ን የተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች የስልጠናው አካል እንደነበሩ ገልጸው የተፈጠረው የዕውቀት ሽግግር የሰው ኃይል ልማቱን ዕውን ለማድረግና የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲዎች የስራ አመራሮች እንዲሁም የስልጠናና ምዘና ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
በቀረበው ሪፖርት መነሻነት በ2019 በጀት ዓመት ለሚሰጠው ስልጠና ትኩረት ሊያገኙ ይገባቸዋል በተባሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይት ተደርጓል ቀጣይ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡ የስልጠናና ምዘና ስራው ውጤታማ እንዲሆን ላደረጉ ተቋማትም የምስጋና እና የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል





