የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት የከተሞች ገቢ ሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ ለፌዴራልና ለክልል የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ
በኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት የከተሞች ገቢ ሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ ለፌዴራልና ለክልል የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ
አዳማ፤ ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም፤ (ከመልሚ)
በከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ በመሬት ልማት እና ካዳስተር እንዲሁም በንብረት ግመታ መሪ ስራ አስፈጻሚዎች በኩል እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራትን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለፌዴራልና ለክልል የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ተሰጠ፡፡
መድረኩን ያስጀመሩት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ተ/ዋና ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ሰሎሞን ጴጥሮስ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት ለከተማ ኢኒሼቲቮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን በማዘመን የከተሞችን የውስጥ ገቢ በዘላቂነት በማሳደግ የከተማ ነዋሪውን የመሠረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላትና የህዝብ አገልግሎትን የተሳለጠ ለማድረግ የሚያስችል አቅምን ለመፍጠር እንዲያስችል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአቅም ግንባታ የስልጠና መርሃ-ግብሩ ላይ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የስልጠና ሠነዶች በፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በተሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች፤ የንብረት ግብር ታክስ አዋጅ ሠነድ፤ የማይንቀሳቀስ የንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ፤ በከተማ መሬት ሊዝ ሲስተምና አተገባበር፤ የከተማ መሬት ይዞታና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ አዋጅ፣ እና በስድስት ዋና ዋና የማዘጋጃ ቤታዊ የገቢ አሰባሰብ ርዕሶች ዙሪያ ቀርቧል፡፡
ለስልጠና በተዘጋጁትና ለውይይት መነሻነት በቀረቡት ስድስት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይት ሂደቱ ለተነሱ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች እና የግልጽነት ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አቅራቢዎችና ከመድረክ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው ከተሞችን በሥርዓት ለመምራት የተዘጋጁ የህግ ማዕቀፎችን ወደ መሬት በማውረድ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት በተዘረጉና በተተገበሩ የሪፎርም ስራዎች ላይ የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ ሀሳቦች በስፋት የተንሸራሸሩበት መድረክ እንደሆነ ከተደረገው የጋራ ውይይት መገንዘብ ተችሏል፡፡










